የተከለሉ ቦታዎች (የግጦሽ ክልከላ ቦታዎች) በአብዛኛው ለአካባቢ መልሶ ማገገም ሲባል በተጎዱ መሬቶች ላይ የሚተገበሩ የመሬት አያያዝ ዘዴ ናቸው። በኢትዮጵያ ሁኔታ የተከለለ ቦታ ማለት እንዲያገግም ከሰውና ከእንስሳት ጣልቃ ገብነት የተጠበቀ የተጎዳ መሬት ማለት ነው። የተከለሉ ቦታዎችን ማቋቋም የተጎዱ ተዳፋት ኮረብታዎችን መልሶ ለማገገም ጠቃሚ ስልት ሆኖ ቆይቷል። በተከለለው ቦታ ውስጥ ምርታማነት በአስደናቂ ሁኔታ ስለሚሻሻልና የአፈር መሸርሸር ስለሚቀንስ ይህ አሠራር ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በተለይ በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች በጣም የተለመደ ሆኗል። የተቋቋሙት የተከለሉ ቦታዎች የተጎዱ የግጦሽ መሬቶችን የዝርያ ስብጥር፣ ብዝሀነትና የባዮማስ ምርት መልሶ በማምጣት ውጤታማ ናቸው፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ በተለምዶ የሥነ-ምኅዳሩ ተግባርና ጤንነት እንዲሻሻል ያደርጋሉ። ቦታን መከለል የተጎዱ መሬቶችን መልሶ ለማገገም ርካሽና ፈጣን ዘዴ ነው። የመሬት መጎዳት ማለት የመሬት ሀብት እየተበላሸ መሄድና በዚህም ምክንያት በዓለም ላይ የእርሻ መሬቶች ዘላቂ የማምረት አቅም መቀነስ ማለት ነው። በመኖ ደጋ፣ ሲዳማ፣ ኢትዮጵያ የተከለሉ ቦታዎች የሚቋቋሙት በግል የግጦሽ መሬቶች ላይ ከመሬቱ ባለቤት አርሶ አደሮች ጋር በሚደረግ ስምምነት ነው። በስምምነቱ ውስጥ አርሶ አደሩ መሬቱን ለአምስት ዓመታት ለመከለል ግዴታ እንደሚገባና በዚሁ ጊዜ ውስጥ በመሬቱ ላይ የሀገር በቀል ዛፎች ችግኞችን እንደሚተክል ተገልጿል፤ በምላሹም ፕሮጀክቱ 5 ዓመታት ሲጠናቀቅ በሄክታር 5000 ብር ማበረታቻ ለመስጠት ይስማማል። ይህም ከፕሮጀክቱ ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል።
የተከለሉ ቦታዎች ባለቤት የሆኑ አርሶ አደሮች በውስጣቸው የዛፍ ችግኞችን ብቻ ሳይሆን የሣር ምርት እንዲጨምር የተሻሻሉ የሣር ዝርያዎችንም ይተክላሉ። የተፈጥሮና የተተከሉ ሣሮች በቤት ውስጥ የሚቀመጡ እንስሳትን ለመመገብ በ«አጭዶ መመገብ» ዘዴ ጥቅም ላይ ይውላሉ። እንስሳትን በቤት ውስጥ መመገብ በክፍት የግጦሽ መሬቶች ሣር ፍለጋ ለመንቀሳቀስ የሚባክነውን ጉልበት ስለሚያድን ጠቃሚ ነው። እንስሳት በቤት ውስጥ ሲመገቡ ይህ ጉልበት እንደ ወተትና ሥጋ ወደመሳሰሉ የእንስሳት ውጤቶች ይለወጣል። እንስሳትን በቤት ውስጥ ስትመግቡ ለ24 ሰዓታት በበረት ውስጥ አታስሯቸውም፤ ይልቁንም ተፈጥሯዊ ባሕሪያቸውንም ማሳየት በሚችሉበት በመኖሪያ ግቢው ዙሪያ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ በነፃነት ትለቋቸዋላችሁ፤ ነገር ግን ወደ የተከለሉ ቦታዎች እንዲገቡ አትፈቅዱም። በቤት ውስጥ የመመገብ ሌላው ጥቅም ከልክ ያለፈ ግጦሽና መረጋገጥ የሚያስከትሉትን የመሬት መጎዳት መከላከሉ ነው።
ይሁን እንጂ በቤት ውስጥ መመገብ ጉዳትም አለው፤ በአጭዶ መመገብ ዘዴ የታጨዱ ሣሮችን ከመሬቱ ብቻ ስለምታወጡ ከመሬቱ ንጥረ-ምግብ የመመናመን ዕድል አለ። ይህንን ክስተት ለማመጣጠን በታጨዱት ሣሮች የወጡትን ንጥረ-ምግቦች ለመተካት የእንስሳት ተረፈ ምርቶችን (ፍግና ሽንት) በተከለሉ ቦታዎች ውስጥ መበተን ያስፈልጋል፤ ይህም የንጥረ-ምግብ ዑደት ይባላል።
የተከለሉ ቦታዎች የማር ምርትን ለመጨመር ለንቦች መኖነት ሊውሉ የሚችሉ በርካታ የሚያብቡ ዕፅዋትንም ይሰጣሉ።
